በክርስቶስ ሰላም ለእናንተ ይሁን!

አስቀድሞ ተሐድሶ ቶውት በሚል በተከታታይ መንፈሳዊ ጽሁፎችን ማቅረብ የተጀመረው በ 2014 እ.ኤ.አ. ሲሆን በዚያ ጦማር ወይም ብሎግ እስካሁን በእግዚአብሔር ፍቃድ የተሰሩ በርካታ  ክንውኖች ናቸው፡፡

በብሎጉ ላይ የሚጻፉት ጽሁፎች በአብዛኛው ድነት ላይ ያተኮሩ ሲሆኑ፡፡  አልፎ አልፎ ከዚያ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሌሎች ቅዱሳን ወንድሞችና እህቶችን የሚጠቅሙ ተሐድሶአዊ መልዕክቶችም ይቀርባሉ፡፡ ለምሳሌ በድነት ዙሪያ ከሚቀርቡት መካከል ሚስጥረ-ድነት ፣ አስቸኳይ መልዕክት ፣ ከሲኦል የተላከ ደብዳቤ ፣ ንስሐ ገብተዋልን? የሚሉ  ይገኙባቸዋል፡፡ በፌስ ቡክ ላይ እንዲቀርብ ታስቦ የተሰሩ በጥበባዊ መንገድ ወንጌልን የሚናገሩ ጽሁፎችም አሉበት:: ለምሳሌ ለቪዛ ፈላጊዎች ፣ ነጻ የትምህርት ዕድል ፣ ክፍት የስራ ቦታ ፣ ዜና ማህደር ፣ የሰርግ ጥሪ… የመሳሰሉት ናቸው፡፡

 ከዚሁ የድነት መልዕክት ጋር የተያያዘ እና የክርስቲያን በዐላትን አስመልክቶ የተጻፉ መልዕከቶችም አሉ፡፡ ለምሳሌ ፋሲካ ፣ የገና መልዕክት ፣ ስለ ስቅለት ፣ ስለ ሰሞነ ህማማት ፣ ታንክስ ጊቪንግ ላይ እና የአዲሱ ዓመት መልዕክቶች የመሳሰሉት ናቸው፡፡ የአበሻው ህብረተሰብ በዓለም ላይ ሁሉ የተበተነ እንደመሆኑ አንዳንድ በዐላት ሁለት ጊዜ የመከበር እድል አላቸው፡፡ ከዚህም የተነሳ እንደየ አውዱ እና የአገራቱ በዐል መሰረት፤ በተለይም በዌስተርን አገሮችና ከራሳችን ባህል አንጻር ተመጣጥነውና ታስቦበት የቀረቡ መልዕክቶች ናቸው፡፡ ከዚሁም ጋር አንዳንዶቹ ወገኖቻችን በውጪ አገር ተወልደው ያደጉ በመሆኑ፡ ከቋንቋ አንጻር  እንዳይቸገሩ ዋና ዋና የድነት መልዕክቶች በእንግሊዝኛ ጭምር ተጽፈው ቀርበዋል፡፡ ለምሳሌ urgent message , Don’t Delay ,the secret of Salvation….ወዘተ ሲሆኑ፡፡ በቀጣይም በኦሮምኛ /ቁቤ/ እና በእስፓኒሽ ቋንቋ ለማስተርጎም ዕቅድ አለ፡፡  በሌሎችም ቋንቋዎች ሁኔታው እንዳመቸ መጠን ለማድረስ ጥረት ይደረጋል፡፡

የቆዩ ክርስቲያኖችን በመንፈሳዊ ህይወታቸው ለማበረታታትና የበለጠ እንዲተጉ ለማስቻል የተጻፉ መልዕክቶችም አሉ፡፡ ለምሳሌ፡- ቀን ሳለ ፣ እግሬን አታጥብም ፣ አገልጋይና አገልግሎቱ ፣ ሰጥቶም ነስቶም ፣ ንገስባት ፣  የእግዚአብሔር አሳብ እና ስለ አራቱ ጨረቃዎች ከመጨረሻው ዘመን ጋር በማያያዝ ተጽፈው ቀርበዋል፡፡

ከዚህ ሌላ የኦርቶዶክስ ህዝባችንን ጥያቄ ከመፍታት አንጻር ሰው ሁሉ በዚህች ቤተክርስቲያን ስላለው የኑፋቄ አስተምህሮ እውነቱን እንዲያውቅ እና ለሌሎችም በጥሞና እንዲያስረዳ በማሰብ የተወሰነ ዕውቀት የሚያስጨብጡ ርዕሶችን በማንሳት በሰፊው ለመጻፍ ተሞክሯል፡፡ በዚህም አመርቂ ውጤት ታይቷል፡፡ ለምሳሌ ፡- ስንት አይነት መጽሐፍ ቅዱስ አለ? የሚል ከአዋልድ መጽሐፍት ጋር ተያይዞ የቀረበ ፣ አማላጅነት የሚል  ስለ ቅዱሳን ምልጃ ፣ የቅዱሳን መላዕክት ድርሻ ፣ ስለ ዝክር ፣ የሙታን ተስካር ፣ ስለ ካህናት ስልጣን ፣ ሚስጥረ ቁርባን..ወዘተ የቀረበ ፤ በቀጣይ ስለ ቀኖና ና ዶግማ  ፣ ጾም በሚል ርዕሶች በተከታታይ የሚቀርቡ ትምህርቶች አሉ፡፡

እስካሁን የወንጌል መልዕክቶችና ፣ ሌሎች ተያያዥ ትምህርቶች በፌስ ቡክ ፣ በኢ-ሜይል ፣ በጉግል ፕላስ ፣ በስልክ ና  በቫይበር ላይ እየቀረቡ  ሲሆን፤ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች መልዕክቱን እያነበቡ እንደሆነ የሚቀርበው ዘገባ ያሳያል፡፡ በአንባቢያን መከታተያ ብሎጉ ላይ እንደሚያሳየው እስካሁን ከ24 በላይ የተለያዩ አገራት ላይ በዓለም ዙሪያ ጽሁፎቹ ደርሰው እየተነበቡ ነው፡፡ እነዚህም በተለይ በአሜሪካ ፣ ኢትዮጵያ፣ ካናዳ ፣ እንግሊዝ፣ ኩዌት ፣ ባህሬን፣ ኔዘርላንድ፣ ሱዳን፣ ፈረንሳይ፣ ፖላንድ፣ ዩክሬን ፣ ግብጽ፣ ጀርመን፣ ስዊዘርላንድ ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኢንዶኔዢያ፣ ብሩንዲ ፣ የመን፣ ጣሊያን፣ ኤርትራ፣ ኖርዌይ፣ ሀንጋሪ፣ ኬንያ ፣

ሩማንያ እና ሳውዲ አረቢያ ለሚኖሩ ወገኖቻችን ደርሶ እየተነበቡ ያሉ ናቸው፡፡

  የሚደርሳችሁን መልዕክት እያነበባችሁ ደግሞ ለወገኖቻችሁ ወደ ተለያየ ዓለም በቴክስት  በመላክ የተጋችሁትን ሁሉ እግዚአብሔር አብዝቶ ይባርካችሁ፡፡ እንደሚታወቀው በአሁኑ ሰዓት በዓለም ላይ 3.17 ቢሊዮን ሰው የኢንተርኔት ተጠቃሚ እንደሆነ በ2015 መጨረሻ ላይ የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በቅርቡ እንደወጣው መረጃ ደግሞ ከ 900 ሚሊዮን በላይ የሆነ ህዝብ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ነው ፡፡ ይህ ማለት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  በማቴዎስ ወንጌል 28፡ 18-20 እና ማርቆስ 16፡15 ‘’ ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ና ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ ንገሩ ብሎ እንዳዘዘ ….’’ በትዕዛዙ መሰረት ይህን ለመተግበር ህዝቡ የት ነው ያለው ? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ይኸው ከላይ እንደተገለጸው ከ 7 ቢሊዮን የዓለም ህዝብ ውስጥ ከ 3 ቢሊዮን በላይ የሚሆነውን ወገን ኢንተርኔት ላይ ነው የምናገኘው ማለት ነው ፡፡በክርስቶስ አምነው  የዳኑ ሰዎች ምን ያህሉ በዚያ ውስጥ እንዳሉ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ለማንኛውም ይህን መንገድ ተረባርበን ካልዋጀነው ሌሎች ገብተው ህዝቡን  ይዘርፉብናል፡፡

  ከአንድ ዓመት የጦማር አገልግሎት በኋላ አሁን ደግሞ በእግዚአብሔር ፍቃድ ለመከሩ ሰራተኞች የሚል አዲስ ዌብ-ሳይት/ ድረ-ገጽ/ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ በውስጡ ትራክቶችን /በራሪ ጽሁፎች በሚለው ሊንክ ውስጥ/፣ በክርስቲያንና አገራዊ በዐላት ወቅት ለመመስከር የሚረዳ ፣ ሌሎች ሐይማኖታዊ ነክ ጥያቄዎችን ተመርኩዞ በሰፊው የተጻፉ ትምህርቶችን ሁሉ በየ ርዕሱ ያገኟቸዋል፡፡ ለስራ አለቃዎ እና ለሌሎች እንግሊዝኛ ተናጋሪ ህብረተሰብ ክርስቶስን ሊያስተዋውቁ ከወደዱ በጥሩ ሁኔታ የተዘጋጀውን መልዕክት ገብተው በቀጥታ በአድራሻቸው መላክ ብቻ ነው፡፡

በተጨማሪ ለመከሩ ሰራተኞች በልዩ ሁኔታ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረበ የነገረ መለኮት መዝገበ-ቃላት በአማርኛ ተተርጉሞ ቀርቦሎዎታል፡፡ ከዚያ ጋር የተያያዙ አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃዎችም ተጭኖልዎታል፡፡ ለቤተክርስቲያን፣ ለሚኒስትሪ አገልጋዮችና ምዕመን ደግሞ አስፈላጊውን የምስክርነት ስልጠና ለመስጠት ማኑዋል መጽሐፍ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ የሚፈልጉ ሁሉ ከሙሉ ማብራሪያው ጋር ያሉበት ቦታ ስልጠናውን ለመስጠት አልያም ማቴሪያሎችን ለማድረስ እንተጋለን፡፡ ስለ ጦማሩም ሆነ ስለ ድረ-ገጹ አጠቃቀም፣ ሰው ሁሉ ያለበት ቦታ ሆኖ እንዴት መልዕክቶችን ወደተለያየ ቦታ መላክ እንደሚችል ጭምር ስልጠና እንሰጣለን በየትኛውም ስፍራ ከምትገኝ የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ጋር እና ሸክሙ ካላቸው ግለሰቦች ጋር በጋራ እንሰራለን፡፡

ዓላማችን ጥቂት ወንጌላውያን ብቻ ሲደክሙበት የነበረውን የወንጌል ምስክርነት እና ስርጭት አገልግሎትን ሁሉም ክርስቲያን በአዲስ እና ቀላል ዘዴ እንዲመሰክሩ ማገዝ እና ስልቱን ማሳየት ነው፡፡ ጌታ በነገር ሁሉ ጸጋውን ያበዛልን ዘንድ ስለ አገልግሎታችን ይጸልዩልን ፡፡ ሁሉም ሰው ስለወንጌል ይኑር ያለንንም ነገር ሁሉ ስለ ወንጌል እናኑር !!!

በጌታ አገልጋያችሁ

ብንያም በፍቃዱ አቦዬ

benjabef@gmail.com


Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *